top of page
Search

ቺኩንጉንያ እና ዴንጊ በኢትዮጲያ አስጊነታቸው ጨምሯል ለመሆኑ  ልዩነታቸውና  ህክምናቸው  ምንድነው?

Updated: Feb 8, 2024

የጤና መረጃ ፣ በየሳምንቱ ይቀርባል 👉 ያድምጡ     AH online radio & Podcast




ቺኩንጉንያ እና ዴንጊ በኢትዮጲያ አስጊነታቸው ጨምሯል ለመሆኑ  ልዩነታቸውና  ህክምናቸው  ምንድነው?


በኢትዮጵያ አዳዲስ የወባ ትንኝ ዝርያዎች  አማካኝነት የሚተላለፉ አዳዲስ  የወረሽኝ በሽታዎች እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡ ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዚህ በፊት በማይታወቁ የወባ በሽታ አምጭ ትንኞች የሚከሰት የወባ በሽታ ዓይነት  እየጨመረ መምጣቱን፤ በፓን አፍሪካን የወባ ትንኝ መቆጣጠሪያ ማህበር የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው ገልጸዋል።  ፕሬዝደንቱ አክለውም፤ የወባ በሽታ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ያልነበሩ እና ጠፍተው የነበሩ ትንኝ ወለድ በሽታዎች በስፋት እየተስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል። “ለአብነትም ደንጊ (Dengue fever) የተባለው በሽታ በስፋት በእስያ አካባቢ ይታወቅ የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያ የበሽታ ታሪክ በፈረንጆች 2013 ለመጀመሪያ ጊዜ ታይቷል፡፡” ካሉ በኋላ፤ በሽታው አድማሱን አስፍቶ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መታየቱን ጠቁመዋል። “በሽታው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ባህሪውን፣ መከላከያ መንገዱ እና የምርመራ ሂደቱ አለመታወቁ ትልቅ የኅብረተሰብ የጤና ችግር ሆኖ መጥቷል፡፡” ነው ያሉት። 


 በኢትዮጲያ ለመጀመሪያ የታየው በሶማሌ ክልል መሆኑን ጠቁመው፤ በመቀጠል በድሬድዋ፣ አፋር፣ መተሃራ፣ አዳማ፣ ወሎ፣ መተማ እንዲሁም በቅርቡ ጎጃም እና ቤኒሻንጉል አካባቢዎች የወባ ስርጭቱ መስፋፋቱን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ተደጋጋሚ ግጭቶች በሽታውን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመቀነስ የሚሰሩ ሥራዎችን በማደናቀፍ የራሱ አስተዋጾ እንዳለው ገልጸዋል። እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ለወባ በሽታ መስፋፋት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አመላክተዋል።  ለመሆኑ ቺኩንጉንያ እና ዴንጊ ልዩነታቸውና  ህክምናቸው  ምንድነው? 



ቺኩንጉንያ / ቺኩን ጉንያ (Chikungunya)

ቺኩንጉንያ በቫይረስ የሚመጣ በሽታ ሲሆን ወደ ሰውም የሚተላለፈው ቫይረሱን በተሸከመች የወባ ትንኝ ንክሻ ነው፡፡ ቺኩንጉንያ (Chikungunya) በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ቦታወች ላይ እየተከሰተ ያለና ምንም አይነት ፀረ-ቫይረስ ክትባትም ሆነ መድሃኒት ሊያድነው የማይችል በሽታ ነው። በሽታውን ልንከላከል የምንችልበት ዘዴ ራሳችን ከትንኝ ንክሻ በመከላከል ነው። በትንኝ ከተነከሰ በኋላ ከ 3 እስከ 7 ቀናቶች ውስጥ ምልክቶች ይታዩበታል።  ቺኩንጉንያ (Chikungunya) ቫይረስ ያለበት በሽተኛ ከ3–7 ቀን የሚቆይ ትኩሳትና ሽፍታ እንዲሁም ከባድ የመገጣጠሚያ ህመም ይኖረዋል። በብዛት የእጅ እና የእግር መገጣጠሚያዎቹ ላይ ህመም፣ የጡንቻ ህመም፣ እንዲሁም የጀርባ ህመም ይስተዋላል። አንዳንድ ሰዎች ከባድ ህመም ሊያጋጥማቸው እንዲሁም ለመንቀሳቀስ፣ ለመቀመጥ ወይም መራመድ ሊቸገሩ፣ አንዳንድ ሰዎች ላይ ደግሞ ሲቆይ ወደ መገጣጠሚያ ብግነት (osteoarthritis) ሊቀየር ይችላል። አንዳንድ በሽተኞች ላይ ደግሞ ምንም ከባድ የሆነ ምልክት አያሳይም ፓራሲታሞል ወይም ሌላ የህመም ማስታገሻ መድሃኒት በመውሰድ ህመሙ በሁለት ሳምንት ውስጥ ይሻሻላል ወይም ሊድን ይችላል። በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች ውስጥ የሚኖረው የህመም ምልክት የተለያየ ነው። ለምሳሌ እድሜያቸው ከሁለት አመት በታች የሆኑ በቺኩንጉንያ (Chikungunya) ቫይረስ የተያዙ ህፃናት ህመሙ ሊፀናባቸው ይችላል። በአንፃሩ ደግሞ እድሜያቸው ከሁለት አመት በላይ የሆኑ ልጆች እንዲሁም ወጣቶች ላይ ትኩሳት፣ ሽፍታ፣ እንዲሁም ከባድ ያልሆኑ የመገጣጠሚያ ህመም ብቻ ሊያስከትል እንዲሁም እድሜያቸው ከገፉና ከውልደት ጀምሮ ያሉ ይበልጥ ጥንቃቄ ይሻሉ፡፡

ቺኩንጉንያ ምልክቶች ምንድናቸው?  ከሰው ወደ ሰው የሚለያዩ ሲሆን፣ የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ፦

  •  በድንገት የሚከሰት ከፍተኛ ትኩሳት (>102°F)

  • ባድ የሆነ የመገጣጠሚያ ህመም በተለይ በክንዶች ወይም እግሮች ላይ

  •   ራስ ምታት

  •   የጡንቻ ህመም

  •   የጀርባ ህመም

  •   ሽፍታ (~50% ተጠቂዎች ላይ የሚያጋጥም)

  ቺኩንጉንያ በወሊድ ጊዜ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላልፍበት እድል እጅግ ዝቅተኛ ነው። ቺኩንጉንያ ከሰዎች ጋር በሚደረግ ግንኙነት፣ ለምሳሌ በንክኪ ወይ መሳሳም አይተላለፍም። ከትንኝ ውጪ በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ምንም አይነት ሪፖርት የለም። ይሁን እንጂ አንዴ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ሰውነታቸው በሽታውን ለመከላከል ኢሚውኒቲ ይኖረዋል ነገር ግን በቀጣይ በበሽታው ላለመያዛቸው ማረጋገጫ የለም። በሽታውን ለመከላከል የተሻለው መንገድ ራስን ከትንኝ ንክሻ መከላከል እንዲሁም በመኖሪያ አካባቢያችን ያሉ የትንኝ መራቢያ ቦታወችን በማጥፋት ትንኝ እንዳይራባ በማስቆም ይመከራል፡፡

የሚከተሉት ሰዎች በትንኝ እንዳይነከሱ ከሌሎች የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

  • ህጻናት (<1 ዓመት)

  • አረጋውያን (>65 ዓመት)

  • እንደ ስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት ወዘተ በመሳሰሉ ስር የሰደዱ በሽታዎች የተጠቁ ሰዎች።


ቺኩንጉንያ ተጠቂቻለሁ የሚል ጥርጣሬ ካደረብኝ ምን ማድረግ አለብኝ? ትኩሳት እና የመገጣጠሚያ ህመም ለመቀነስ የሚረዱ መድሀኒቶችን  (ከአስፕሪንና አይቢዩፕሮፌን ውጪ የሆኑ) መጠቀም ጥቅም ሊኖረው ይችላል።  እንዲሁም የታይብዎ ምልክቶችን መዝግበው በመያዝ ሐኪም ያማክሩ። ራስዎን ተጨማሪ በትንኝ ከመነከስ ይከላከሉ። ቆዳዎን በየቀኑ ቀኑን ሙሉ ጸረ ትንኝ ቅባት ይቀቡት ፣ረዥም፣ ቀለል ያለ እና ቀላል ቀለም ያለው ልብስ ይልበሱ። እቤት ውስጥም ከቤት ውጪም ያለ ማንኛውም ያቆረ ውሃ ያስወግዱ። ማታና ጠዋት ትንኞች በብዛት የሚንቀሳቅሱበት  ጊዜ በመሆኑ በተቻለ መጠን ከቤት አይውጡ።



ዴንጊ / ደንጊ (Dengue fever)

ዴንጊ በዴንጊ ቫይረስ የሚመጣ የቫይረስ ኢንፌክሽን ሲሆን ቫይረሱን በያዘች ኤዴስ በተባለች  የትንኝ ንክሻ ወደ ሰዎች ይተላለፋል። በአንዳንድ አገሮች ኤዪዲስ አልቦፒክተስ እንደተባሉ ያሉ ሌሎች የትንኝ ዝርያዎችም የዴንጊን ቫይረስ ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ዴንጊ ይበልጥ ተስፋፍቶ የሚገኘው ሞቃታማና ከፊል ሞቃታማ በሆኑ አካባቢዎች ሲሆን በተለይ ደግሞ በዝናባማ ወራት ብሎም እንደ ጎርፍ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ከደረሱ በኋላ ባሉት ወቅቶች ስርጭቱ ይጨምራል። ይህ የሆነው እንስቷ ትንኝ እንቁላሎቿን የምትጥለው ውኃ ባቆሩ ቦታዎች ስለሆነ ነው።

 በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን ደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች ለቤት አገልግሎት የሚያውሉትን ውኃ የሚያጠራቅሙት በገንዳዎች ውስጥ ስለሆነ የጤና ባለሙያዎች ገንዳዎቹን እንዲከድኑ ለሕዝቡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ይሰጣሉ። እንዲህ ማድረግ ገንዳዎቹ የትንኝ መራቢያ እንዳይሆኑ ይከላከላል። በተጨማሪም ሰዎች ከግቢያቸው አሮጌ ጎማዎችን፣ ጣሳዎችን፣ የአትክልት መትከያዎችንና የፕላስቲክ ዕቃዎችን ጨምሮ ውኃ ሊያቁሩ የሚችሉ ማናቸውንም ነገሮች ካስወገዱ እነዚህ ትንኞች እንዳይራቡ መከላከል ይችላሉ።

የዴንጊ ምልክቶች

  • ትኩሳትና ራስ ምታት

  • ጡንቻ እና የመገጣጠሚያ ህመም

  • ማቅለሽለሽ, ማስታወክ እና የባህሪ ሽፍታ

  • በአንዳንድ ሁኔታዎች የደም መፍሰስን (ከባድ የዴንጊ ሄመሬጂክ ትኩሳት -DHF)

  • ዝቅተኛ የደም ግፊት እና ሞት ሊያስከትል ይችላል፡፡

የዴንጊን ምልክቶች ለይቶ ማወቅና በሽታውን መቋቋም

ዴንጊ የሚያሳያቸው የሕመም ምልክቶች ከኢንፍሉዌንዛ ጋር በጣም ስለሚመሳሰሉ ብዙ ጊዜ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ላይረዱ ይችላሉ። ይሁንና የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ አንድ ሰው ከትኩሳት ጋር ተያይዞ ቆዳው ላይ ሽፍታ ከወጣበት፣ በውስጠኛው የዓይኑ ክፍል ሕመም የሚሰማው ከሆነ እንዲሁም የጡንቻ ሕመም ካለውና መገጣጠሚያውን በኃይል የሚቆረጣጥመው ከሆነ (አጥንት ሰባሪ ትኩሳት ተብሎም የሚጠራው ለዚህ ነው) በዴንጊ በሽታ ተይዞ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ይኖርበታል። ትኩሳቱ ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ሊቆይ ይችላል። 


ዶክተሮች እስከ ዛሬ ለዴንጊ በሽታ መድኃኒት ባያገኙም አብዛኛውን ጊዜ እረፍት በማድረግና ብዙ ፈሳሽ በመጠጣት ራስን በራስ ማከም ይቻላል። ይሁን እንጂ በሽታው ዴንጊ ሾክ ሲንድሮም ወደሚባል ደረጃ ወይም ሄመሬጂክ ፊቨር ወደተባለ ደም መፍሰስ የሚያስከትል ኃይለኛ ትኩሳት ሊያድግ ስለሚችል ሕመምተኛው በቂ ክትትል ሊደረግለት ይገባል። ለሞት ሊያደርሱ የሚችሉት እነዚህ የሕመም ደረጃዎች ግለሰቡ የመጀመሪያው ትኩሳት ጋብ ካለለት በኋላም ወይም እየተሻለው እንደሆነ በሚሰማው ጊዜም ሊታዩ ይችላሉ። በሽታው እዚህ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ አንዳንድ ምልክቶች ምንድን ናቸው? በሽተኛው ኃይለኛ የሆድ ሕመም ሊሰማው፣ ለረጅም ጊዜ ሊያስመልሰው፣  ነስር እና የድድ መድማት ሊያጋጥመው፣ ዓይነ ምድሩ ሊጠቁርና ቆዳው ላይ የበለዘ መልክ ያለው እባጭ ሊወጣበት ይችላል። በተጨማሪም መቅበጥበጥ፣ ከመጠን ያለፈ የውኃ ጥም፣ የቆዳ መገርጣትና የሰውነት መቀዝቀዝ እንዲሁም በጣም ዝቅተኛ የሆነ የደም ግፊት የዴንጊ ሾክ ሲንድሮም ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ።


ዴንጊ በባክቴሪያ ሳይሆን በቫይረስ የሚመጣ በሽታ በመሆኑ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን መውሰድ ምንም ጥቅም የለውም። በተጨማሪም እንደ አስፕሪንና  አይቢዩፕሮፌን ያሉ የሕመም ማስታገሻዎች ይበልጥ ለደም መፍሰስ አደጋ ስለሚያጋልጡ ሕመምተኛው እነዚህን መድኃኒቶች ባይወስድ የተሻለ ነው። በአማራአጭነት እንደ ፓራስታሞን ያሉትን ህምም ማስታገሻዎችን መወሰድ ይመከራል፡፡ አራት ዓይነት የዴንጊ ቫይረሶች በመኖራቸው አንድ ሰው ከአንድ ጊዜ በላይ የዴንጊ በሽታ ሊይዘው ይችላል።

የመራቢያ ቦታዎች

  • የተጣሉ ጎማዎች

  • የዝናብ መውረጃ አሸንዳዎች

  • አበባ የተተከለባቸው ዕቃዎች

  • የፕላስቲክ ዕቃዎች

  • የተጣሉ ጣሳዎችና በርሜሎች

የህክምና እና መከላከያ መንገዶች

ለዴንጊ የተለየ ሕክምና የለም:: በሽታውን ለመከላከል ከሁሉ የተሻለው መንገድ ትንኞች እንዳይነክሱ ማድረግ ነው.  በዴንጊ ከተያዝክ በደንብ እረፍት አድርግ፤ እንዲሁም ብዙ ፈሳሽ ውሰድ። በተጨማሪም ትንኞቹ እንዳይነክሱህና በሽታውን ወደ ሌላ ሰው እንዳያዛምቱ በተቻለ መጠን ስትተኛ አጎበር ተጠቀም። ይሁንና መጀመሪያውንም በሽታው እንዳይዝህ፣ በትንኞቹ የመነደፍ አጋጣሚህን መቀነስ የምትችለው እንዴት ነው?


ረጅም እጅጌ ያለው ልብስ፣ ረጅም ሱሪ ወይም ረጅም ቀሚስ መልበስ እንዲሁም ትንኞቹን የሚያባርሩ ነገሮችን መጠቀም ሊረዳ ይችላል። ትንኞቹ በማንኛውም ሰዓት ሊነድፉ ቢችሉም ይበልጥ ንቁ የሚሆኑት ግን ፀሐይ ከወጣች በኋላ ባሉት ሁለት ሰዓታት እና ፀሐይ ከመግባቷ በፊት ባሉት ሁለት ሰዓታት ውስጥ ነው። በተጨማሪም በምትተኛበት ጊዜ የትንኝ ማባረሪያ መድኃኒት የተረጨ አጎበር ተጠቀም።  አብዛኛውን ጊዜ፣ ኤዪዲስ የሚባሉት ትንኞች ከተፈለፈሉባቸው ቦታዎች ርቀው የሚሄዱት ግፋ ቢል ጥቂት መቶ ሜትሮች ብቻ ነው። ስለዚህ የመራቢያ ቦታዎችን በመለየት እርምጃ ውሰድ ያስፈልጋል፡፡


የቺኩንጉንያ እና ዴንጊ ልዩነታቸውን አስተዋሉ?

 ቺኩንጉንያ - ለሳምንታት በሚቆይ የመገጣጠሚያ ህመም የሚታወቅ ሲሆን በአብዛኛው ገዳይ አይደለም፡፡

ዴንጊ - የውስጥ አካላት ስራ እንዲያቆሙ የሚያደርግ በውስጥ የደም መፍሰስ የሚታውቅ ሲሆን አልፎአልፎ ለሞት ይዳርጋል፡፡





 
 
 

Comments


Post: Blog2 Post
bottom of page