top of page
Search

የትኋን ወረሽኝ ስጋት ኦሎምፒክን በምታዘጋጀው ፈረንሳይ

Updated: Jan 26, 2024

ከዕለቱ ዜናዎችና መረጃዎች የተቀነጨበ 👉 ያድምጡ     AH online radio & Podcast



ፓሪስን ጨምሮ በተለያዩ የፈረንሳይ ክፍሎች የተከሰተው የትኋን ወረርሽኝ አገሪቱ በተጣይ የአውሮፓውያን ዓመት በምታስተናግደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የጤና እና የደኅንነት ጥያቄን አስከትሏል።

ባለፉት ሳምንታት በአገሪቱ የትኋን ቁጥር መጨመሩን ብዙዎች ተመልክተዋል።

በማርሴይ ዋና ሆስፒታል ኢንቶሞሎጂስት የሆኑት ዢን ሚሼል በረንገ “በሞቃታማ ወራት የትኋኖች ቁጥር በጣም ሲጨምር እናያለን” ብለዋል። “ዋናው ምክንያት ደግሞ ሰዎች በሐምሌ እና በነሐሴ ወራት ከሚያደርጉት ጉዞ በኋላ ትኋኖቹን በሻንጣቸው ይዘው ስለሚመለሱ ነው” ብለዋል። አክለውም “በዚህ ዓመት የታየው የተባዮቹ ወረርሽኝ መጨመር ካለፈው የበለጠ ይሆናል” ሲሉ አመልክተዋል።

የፓሪስ ቤት አከራዮች ቤታቸው በትኋን እንዳይወረር ስጋት ውስጥ እየወደቁ ነው።

በቅርቡ ትኋኖች በአገሪቱ ሲኒማ ቤቶች ተስፋፍተዋል የተባለው ሪፖርት አለመረጋገጡ ታውቋል። ባቡር ላይም በትኋኖች ተነከስን የሚሉ ስሞታዎች በዝተዋል።

የፓሪስ ማዘጋጃ ቤት እና የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስተዳደር የትኋን ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚያስችል እርምጃ እንዲወስዱ ጥያቄ እየቀረበላቸው ነው። የሚወሰደው እርምጃም ከወራት በኋላ ከሚካሄደው የ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ በፊት ጉዳዩን ምን ያህል በትኩረት እንደሚመለከቱት እና የፓሪስን ገጽታ እንዴት እንደሚጠብቁ የሚታይበት አጋጣሚም ነውም ተብሏል። የተባዮቹን ወረርሽኝ በተመለከተ አስፈሪ ታሪኮች በበይነመረብ ላይ በፍጥነት እየተሰራጩ ጉዳዩን ወደ ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋነት እየቀየሩት ነው።


አልጄሪያ እና ሞሮኮ የቱኋን ወረርሽኝ ከፈረንሳይ ወደ ግዛታቸው እንዳይገባ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ተገልጸ፡፡


ሰሜን አፍሪካውያኑ አገራት አልጄሪያ እና ሞሮኮ በፈረንሳይ የተከሰተውን አሳሳቢ የቱኋን ወረርሽኝ ለመከላከል በድንበር መተላለፊያቸው ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አዘዙ።

የሁለቱ አገራት የጤና ባለሥልጣናት የቱኋን ወረርሽኝ ከፈረንሳይ ወደ አገራቸው እንዳይዛመት ለመከላከል የጤና ቁጥጥር እና የማጽዳት ተግባር ማከናወን መጀመራቸውን አሳውቀዋል።

በዚህም መሠረት ሰዎች፣ መኪኖች፣ አውሮፕላኖች እና መርከቦች ከፈረንሳይ ተነስተው ወደ አገሮቻቸው በሚገቡባቸው መተላለፊያዎች በኩል ተባዮቹ እንዳይዛመቱ ለማድረግ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

ይህ የአልጄሪያ እና የሞሮኮ ውሳኔ ይፋ የሆነው በርካታ ሰዎች የቱኋን ወረርሽኝ ተከስቶባታል ከተባለችው አውሮፓዊት አገር በሚገቡበት ጊዜ ተባዩ አብሮ ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት በመፈጠሩ ነው። አገራቱ የቱኋን ወረርሽኙን ለመከላከል የቅድሚያ መስጠንቀቂያ እና የመከላከል እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንጂ ወረርሽኙ በግዛታቸው ውስጥ ስለማጋጠሙ ያሉት ነገር የለም።



 
 
 

Comments


Post: Blog2 Post
bottom of page