top of page
Search

በእናቷ ማህጸን ሁለተኛ ልጇን ያረገዘችው አውስትራሊያዊት

Updated: Oct 4, 2023

ከዕለቱ ዜናዎችና መረጃዎች የተቀነጨበ 👉 ያድምጡ AH online radio & Podcast



የ30 አመቷ ክሪስቲ ብሪያንት የመጀመሪያ ልጇን ስትወልድ ማህጸኗ በመጎዳቱ በቀዶ ህክምና የእናቷን ማህጸን ወስዳለች:: በቀዶ ህክምና የአንዱን ማሕጸን ወደ ሌላ ማዛወር በፈረንጆቹ 2012 መጀመሩ ይታወሳል በቀዶ ህክምና የእናቷን ማህጸን ያገኘችው አውስትራሊያዊት በተወለደችበት ማህጸን ሁለተኛ ልጇን ማርገዟ ገልጻለች።

ክሪስቲ ብሪያንት የተባለችው የኒው ሳውዝ ዌልስ ነዋሪ በ2021 ነበር የመጀመሪያ ልጇን በድንገት ስትወልድ በማህጸኗ ላይ ጉዳት የደረሰባት። ጉዳቱ ክሪስቲ እና ባለቤቷ ኒክ ሁለተኛ ልጅ ማግኘት እንዳይችሉ የሚያደርግ ነበር። እናም ክሪስቲ ለእናቷ ፈራ ተባ እያለች አንድ ጥያቄ ተንሳለች፤ ማህጸንሽን ስጭኝ የሚል። እናት ሚሼልም ክሪስቲን ዘጠኝ ወር ተንከባክቦ ያቆየውን ማሕጸናቸውን ለልጅ ልጃቸው መወለጃ ይሆን ዘንድ ለመስጠት ምንም አልሰሰቱም። በጥር ወር 2023ም በሲድኒ ሮያል ሆስፒታል 15 ስአት በወሰደ ቀዶ ህክምና የእናት ሚሼል ማሕጸን ወደ ልጅ ክሪስቲ ተዘዋወረ። ከሰሞኑም ክሪስቲ ከእናቷ ባገኘችው ማሕጸን የሰባት ሳምንት ጽንስ መያዟን አብስራ ቤተሰቡ በደስታ ተሞልቷል። “በድጋሚ ጽንስ መያዝ በመቻሌ ደስታዬ ወደር የለውም፤ እናቴም ውድ ስጦታ ስለሰጠችኝ አመሰግናለሁ” ማለቷንም ዴይሊሜል ዘግቧል።

ክሪስቲ ከእናቷ በተሰጣት ማህጸን የያዘችው ጽንስ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገለት ሲሆን፥ በያዝነው የፈረንጆቹ አመት መጨረሻ ሁለተኛ ልጇን እንደምትገላገል ይጠበቃል። የ30 አመቷ አውስትራሊያዊት በቀጣይም ሶስተኛ እና አራተኛ ልጆችን ለመውለድ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች። በቀዶ ህክምና የአንዱን ማሕጸን ወደ ሌላ ማዛወር የተጀመረው በፈረንጆቹ 2012 ነበር። እስካሁንም 90 የተሳካ የማህጸን ዝውውር ቀዶ ህክምና የተደረገ ሲሆን፥ 50 ህጻናትም በዚሁ ዘዴ ተወልደዋል።




18 views0 comments

Comments


Post: Blog2 Post
bottom of page