top of page
Search

‘በኦንላይን’ ( በኢንተርኔት አማካይነት)  አሰሪዎችን በማግኘት ስራ እንዴት መስራት የቻላል?

ከዕለቱ ዜናዎችና መረጃዎች የተቀነጨበ 👉 ያድምጡ     AH online radio & Podcast




‘በኦንላይን’ ( በኢንተርኔት አማካይነት)  አሰሪዎችን በማግኘት ስራ እንዴት መስራት የቻላል?

‘በኦንላይን’ ሥራ እንዴት ገንዘብ ማግኘት ይቻላል? “በ9 ወር ሚሊየነር ሆኛለሁ” የሚለው ኢትዮጵያዊ


የ26 ዓመቱ ናትናኤል በኮምፒውተር ሳይንስ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተመርቋል። ‘በኦን ላይን ቢዝነስ’ [በኢንተርኔት አማካይነት የሚሠራ ሥራ] በዚህ ሥራ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘት እንደቻለ ይገልጻል። እንዴት?


ናትናኤል ተፈሪ አባቱ በጠና ሲታመሙ ግን እርሳቸውን ለማስታመም ሥራ ማቆም ግድ ሆነበት። ሥራ ከጀመረባት ባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። በዚህ መካከል፣ ጓደኛው ቤት ሆኖ ሊሠራበት የሚችለውን ድረ ገጽ ጠቆመው ይህ ድረ ገጽ ‘አፕወርክ’ (upwork) ይሰኛል። በ‘አፕወርክ’ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሥራ ፈላጊዎች ከአሠሪዎች ጋር ይገናኛሉ። እዚህ ላይ ያሉ ሥራዎችን “እሠራቸዋለሁ ብዬ ካሰብኩ ፕሮፖዛል እልክላቸዋለሁ። አሪፍ አድርጌ መሥራት እንደምችል ያመኑበት ሰዎች ያናግሩኛል” ሲል ይጠቅሳል ናትናኤል።


ናትናኤል የመጀመሪያው ሥራውን ያገኘው ከለንደን ነበር። እዚያ ያለ አንድ ደንበኛ በድረገጹ አማካኝነት አጫጭር ቪዲዮዎችን ‘ኤዲት’ የሚያደርግለት ሰው ሲፈልግ ነበር። ናትናኤል ይህንን ሥራ መሥራት እንደሚችል አመነ። ከሰውዬው ጋር ተጻጻፉ፣ ሥራውን መሥራት እንደሚችል አሳመነው። ሥራው ደንበኛው ቀርጾ የላከውን የማስተማሪያ ቪዲዮ ኤዲት ማድረግ እና ተጨማሪ የምሥል መረጃዎችን አካቶ መልሶ መላክ ነው።


ናትናኤል አፕወርክ፣ ሊንክዲን እና ፋይቨር በተባሉ ድረገጾች አማካኝነት ሥራ ያገኛል፡፡ ለዚህ ሥራ መነሻ ገንዘብ አላስፈለገውም። ‘አስተማማኝ’ የሆነ ኮምፒውተርም ሆነ ኢንተርኔት አልነበረውም። “ዩኒቨርሲቲ ስገባ በገዛሁት አሮጌ በሆነ ላፕቶፕ ነበር የጀመርኩት” ይላል። ኢንተርኔት ለማግኘት ደግሞ “ዋይፋይ ያላቸው ሰዎች ቤት ወይም ካፌ” ይሄድ ነበር።

ናትናኤል የመጀመሪያውን ሥራ 40 ዶላር ወይም በዚያን ጊዜ በነበረው ይፋዊ ምንዛሪ 2 ሺህ ብር አካባቢ አግኝቶበታል። እዚህ ጋ፣ ናትናኤል ካገኘው ገንዘብ በላይ “በጣም ጠቅሞኛል” የሚለው ደንበኛው በድረ ገጹ አምስት ኮከብ እና እጅግ አበረታች አስተያየት መስጠቱን ነው። “‘በጣም ግሩም ሥራ ነው። ሌሎችም ከእርሱ ጋር እንድትሠሩ እመክራለሁ’ የሚል አስተያየት ሰጥቶኛል፥ በጣም ነበር ደስ ያለኝ” ይላል። በዚህም ገርበብ ያለው የሥራ ዕድል ወለል ብሎ ተከፈተ። አሁን ከ‘አፕ ወርክ’ በተጨማሪ ‘ፋይቨር’ እና ‘ሊንክዲን’ በተሰኙ ሥራ ማፈላለጊያዎች አማካይነት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው። ከቤቱ መውጣት ሳይጠበቅበት አሜሪካ፣ ስፔን፣ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እና ዱባይ ያሉ ሥራዎችን እየሠራ ‘ጠቀም ያለ’ ገንዘብ ያገኛል። ከዚያም አልፎ ሦስት ሰዎችን ቀጥሮ ማሠራት ጀምሯል። “ባለውለታዬ” የሚለው እና ሰባራ ላፕቶፑን ከፍተኛ ፍጥነት ባላቸው ‘ውድ’ ሦስት ኮምፒውተሮች ቀይሯል። ልብ በሉ! ይህ ሁሉ የሆነው ዘጠኝ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።


“ቢዝነሱ የእኔንም የቤተሰቤንም ሕይወት በሆነ ደረጃ ቀይሮታል” የሚለው ናትናኤል “በኦንላይን ሥራ ብቻ ምንም ሳላወጣ፣ ከቤቴ ሳልንቀሳቀስ፣ ከአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ ሠርቻለሁ። አሁንም እየሠራሁ ነው። የኢንተርኔት እና የመብራት ችግር ነው እንጂ ከዚህ በላይ እሰራ ነበር” ሲል ገልጿል። ተከታታይ ሥራ የሚሰጡትን ደንበኞችንም አፍርቷል። “አንድ ደንበኛዬ ሀበሻ ነው ከዩኬ መጥቶ ቤተሰቤን ጠይቋል። በርቱ ብሎን ሄዷል። አሁንም አብረን እየሠራን ነው” ይላል። በድረገጾቹ አማካኝነት ቪዲዮ ኤዲትንግ፣ ግራፊክስ ዲዛይን እና ተንቀሳቃሽ ካርታ (map animation) የሚያሠሩ ደንበኞችን እያገኘ ከ5 እስከ 1 ሺህ ዶላር ያገኛል። የሚገርመው፣ እነዚህን ሥራዎች በሙሉ ዩቲዩብ እየተመለከተ የተማራቸው ናቸው።

ናትናኤል “በኦንላይን ገንዘብ ለመሥራት አንድ ስልክ በቂ ነው” ይላል። በእነዚህ ሥራ ማፈላለጊያዎች አማካኝነት “ኮምፒውተር ሳያስፈልገን በቀላሉ መሥራት የምንችላቸው ብዙ ሥራዎች” እንዳሉም ይናገራል። ለአብነት፣ አንዳንድ ሰዎች አጫጭር ድምጾች (voice over) እንዲነበብላቸው ድረገጾቹ ላይ ሰው ያፈላልጋሉ። ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገው ድምጽ የሚቀርጽ ስልክ ብቻ ነው። “የቀረጽነው ድምጽ ጥሩ ባይሆን እንኳን [ድምጹን] ማስተካከል የሚችሉ ነጻ ድረገጾች (ዌብሳይቶች)”እንዳሉ ይጠቅሳል። ሌሎች ደንበኞችደግሞ መረጃየሚያሰባስብላቸው ሰው ሊፈልጉ ይችላሉ። ስልክ እና ኢንተርኔት ያለው ሰው መረጃዎችን ከኢንተርኔት ላይ እየፈለገ ማስገባትም (Data entry) በቀላሉ ሊሠሩ ከሚችሉ ሥራዎች አንዱ ነው።


ናትናኤል መጀመሪያ ‘በኦንላይን’ ገንዘብ የሠራው በ‘አፕ ወርክ’ ነው። አሁን ከዚያም አልፎ ‘በፋይቨር’ እና ‘ሊንክድኢን’ አማካኝነት ሥራ ያገኛል። በ‘አፕወርክ’፣ ‘ፋይቨር’ እና ‘ሊንክዲን’ ድረገጾች በትርፍ ወይም በሙሉ ጊዜ የሚሠሩ በሺዎች የሚቀጠሩ ሥራዎች አሉ። መሥራት የሚፈልጉ ሰዎች ክህሎታቸውን፣ የሥራ ልምዳቸውን እና ሌሎች መረጃዎችን በእነዚህ ድረገጾች አማካኝነት ይጭናሉ። ተመሳሳይ ገጾቹ ላይ ማሠራት የሚፈልጉ ግለሰቦች ወይም ኩባንያዎችም ይገኛሉ። አሠሪዎች ከሚያወጡት ማስታወቂያ ስር ሥራ ፈላጊዎች የሚያስከፍሉትን የገንዘብ መጠን ያስቀመጣሉ። አሰሪው የሥራ ፈላጊውን መረጃዎች እና የገንዘብ መጠን አይቶ ‘ያዋጣኛል’ ላለው ሥራውን ይሰጣል። ይህንን የመሰሉ በርካታ ድረገጾች አሉ። ችግሩ ሁሉም ትክክል አይደሉም አንዳንዶቹ ለቀማኛ አሳልፈው ይሰጣሉ። አንዳንድ አጭበርባሪዎች ደግሞ በትክክለኞቹ ገጽ በኩል ሊመጡ ይችላሉ።

አጭበርባሪዎች በሥራ ድረገጾች አማካኝነት ሥራ ፈላጊዎችን ዒላማ እንደሚያደርጉ ቢቢሲ በአንድ ወቅት ያገኘው መረጃ አመልክቷል። ሊንክንዲን ሐሰተኛ ‘አሰሪ ነን ባዮችን’ የሚያስወግደበት አሠራር መዘርጋቱንም ጠቅሷል። ያኔ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቅጥር እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ አጭበርባሪዎች በብዙ መንገድ እንደሚመጡ አስረድተዋል። ሁሉም ባለሙያዎች ሥራ ፈላጊዎች ሥራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ‘ቀጣሪ ነን’ የሚሉ ኩባንያ ወይም ግለሰቦች ትክክለኛ መሆናቸውን እንዲያጣሩ ይመክራሉ። የናትናኤልም ሀሳብ ተመሳሳይ ነው።“የምንሠራበትን ዌብሳይት ትክክለኝነት ሳናረጋግጥ ሥራ ከጀመርን እና ችግር ከገጠመን ተስፋ እንድንቆርጥ እና ሌሎችን እንዳናምን ነው የሚያደርገን” ይላል። ቀጥሎም “ማንኛውንም ሥራ ከመጀመራችን በፊት 10 ደቂቃ ወስደን [ሰለ ድረገጹ] ብናጣራ ሁሉንም ማወቅ እንችላለን። ያየነውን ሁሉ ማመን የለብንም፤ ማጣራት ይኖርብናል” ሲል ገልጿል።


የኦንላይን ሥራ ትጋት ይፈልጋል፡፡ ናትናኤል በኦንላይን የሚሠሩ ሥራዎች ጥሩ ገንዘብ ቢሠራባቸውም ትዕግሥት እንደሚፈልጉ ይገልጻል። አሁን እኔ ከጓደኞቼ ጋር የምዝናናበትን ጊዜ ቀንሼ፣ ከቤተሰቤ ጋር በደንብ ጊዜ ማሳለፍ ብፈልግም እሱንም ቀነስ አድርጌ፣ እንቅልፌን ቀነስ አድርጌ ነው የምሠራው። የወደፊቱን ለማሳካት ያለኝ አማራጭ ትጉህ መሆን ብቻ ነው” ይላል። ቀጥሎ “በምንም ነገር ተስፋ አልቆርጥም” ሲል ጨምሯል። በሥራዎቹ ያዳበረው ትጋት እና ተስፋ አለመቁረጥ ወደፊት ሩቅ ለሚያስብበት ‘የኦንላይን ቢዝነስ’ እጅግ እንደጠቀመው ይናገራል።




4 views0 comments

댓글


Post: Blog2 Post
bottom of page