ከዕለቱ ዜናዎችና መረጃዎች የተቀነጨበ 👉 ያድምጡ AH online radio & Podcast
ንቦችን እንደ ሸማ የሚለብሰው ኢትዮጲያዊው ወጣት አገሩን በድንቃድንቅ መዝገብ የማሰፈር ብርቱ ፍላጎት አለው
ገና አፍላ ወጣት ነው፤ ከወገቡ በላይ ራቁቱን ሆኖ ንቦችን እንደ ሸማ ለብሷቸው ይታያል። እጁ፣ ጆሮውም ላይ ሆነ አፍንጫው ላይ መከላከያ አላደረገም። እነርሱም እንዲሁ በላዩ ላይ ይርመሰመሳሉ። ይህ ለሚመለከተውም ለሚሰማውም ግራ የሆነ ነገር እንዴት ሊሆን ቻለ? ሲል ተጠይቋል፡፡ “ስጦታ ነው” ከማለት ውጪ ተጨማሪ ማብራርያ የለውም። ሰሚ ሁሉ የታምራትን ንብ የማላመድ ስጦታ ማየቱ እና መስማቱ አስደንቆታል። እርሱም “ተሰጥኦዎዬ ንብ ማነብ ነው። እነርሱ ደግሞ ይታዘዙኛል” ይላል።
ታምራት ጌታቸው 18 ዓመቱ ነው። ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አሶሳ ከተማ ነው ተወልዶ ያደገው። በንብ ማነብ ስራ ነው የሚተዳደረው። ታምራት ንብ ማነብ የጀመረው ከአምስት ዓመት በፊት ነው። መጀመርያ የራሱ ንብ አልነበረውም። ሌሎች ንብ የሚያንቡ ጎረቤቶቹን ሲመለከት ከንብ ጋር መላመድ ጀመረ። “ንቦች ለቀረቧቸው እንደ ሰው ናቸው” የሚለው ታምራት ሌሎች የሚያንቧቸው ንቦች ጋር በሚያልፍበት ወቅት መጥተው ላዩ ላይ እንደሚያርፉ እርሱም በዚህ አንግዳ ነገር እንዳልተደናገጠ ያስታውሳል። “እኔ የማወራውን ይሰሙኛል” የሚለው ታምራት “ተግባብተን ነው ያለነው” ሲል ያክላል። ይህንን የተመለከተው ታምራት ንብ ወደማነብ ገባ።
“ንቦች ከነደፉ ይገድላሉ”የሚለው ታምራት፣ በንብ ተነድፎ የሞተ ሰውም ተመልክቶ ያውቃል። አገሬው ማር ለመቁረጥ፣ በጨለማ ወይንም ጢስ ይዞ እንጂ እንዲህ ታምራት እንደሚያደርገው በባዶ እጅ ያለምንም መከላከያ ማንም ወደ እነርሱ አይጠጋም። ታምራት በሄደበት ንቦች እርሱ ጋር መጥተው ሲከቡት እና ሲከተሉት “ይህ የፈጣሪ ስጦታ ነው” ከማለት ውጪ ሌላ መጨመር አልቻለም። ታምራት ከእርሱ ውጪ እንዲህ ንብ ለምዶት፣ እርቃን ገላውን ሁሉ ለብሶት ያየው ሰው ኢትዯጵያ ውስጥ የለም። በርግጥ ስማቸውን በድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ያስመዘገቡ የሌላ አገር ዜጎች መኖራቸውን ያውቃል። ግን ለመጀመርያ ጊዜ ንቦቹ መጥተው በላይ ላይ እነዳሻቸው ሲርመሰመሱ ምን ተሰማው? “አልፈራሁም። በአማርኛ ሂዱ ስላቸው ሄዱ። እጄ ላይ ሁኑ፣ ሰውነቴ ስላቸው ይሰማሉ፤ ይቀመጣሉ። ሰው ይህንን ሲያይ መጀመርያ ላይ ፈርቶ ነበር፤ ሌሎች ደግሞ ተው ይሉኝ ነበር። እየቆየ ሲመጣ ግን ስጦታ መሆኑ ሰዉ እየገባው መጣ።” ይላል።
ታምራት አሁን ሦስት የንብ ቀፎ አለው። ተጨማሪ ቀፎዎችን አሰናድቶ የሚገቡ ንቦችን እየተጠባበቀ ነው። ታምራትን ቤተሰቦቹ አሁን ይደጉፋታል። “ንቦች ጋር ስትቀርብ ንጹህ መሆንአለብህ”የሚለው ታምራት አፉ ውስጥ እንደሚገቡ እና ወደ ጉሮረው እንዳይገቡ ሲነግራቸው እነደሚሰሙት ያብራራል። “ተዉ ወደ ጉሮሮዬ አትግቡ ስላቸው አይገቡም። ስጠራቸው ይመጣሉ። ሂዱ ስላቸው ይታዘዛሉ።” ያለው ታምራት ነድፈውት ያውቁ እንደሆነተጠይቆሲመልስ“ተነድፌ አውቃለሁ። እነርሱ ፊቴ ላይ ተቀምጠው ላወርዳቸው ስል በእጄ ስጫናቸው ነው ነድፈውኝ የሚያውቁት። ግን ለመንደፍ ብለው አይደለም።”ታምራት ራሱንም ሆነ አገሩን በድንቃድንቅ መዝገብ የማሰፈር ብርቱ ፍላጎት አለው። ኢትዮጵያኖች “እኔስ በአገሬ እንኳን ሰው ወፍ አለምዳለሁ”ን ሲዘፍኑ፣ እርሱ ደግሞ እንኳን ሰው ንብ አለምዳለሁ ብሎ መታወቅ ብርቱ መሻቱ ነው።
Comentarios