top of page
Search

ገቢ ለማግኘት 500 ‘ሰብስክራይበር’ ይበቃል;ዩቲዩብ

Updated: Oct 4, 2023

ከዕለቱ ዜናዎችና መረጃዎች የተቀነጨበ 👉 ያድምጡ AH online radio & Podcast



በ2021 ዩቲዩበሮች 300 ሚሊዮን ዶላር ወደ ኪሳቸው አስገብተዋል።ይህ ገቢ በዋናነት ከማስታወቂያ የሚገኝ ነው። ዩቲዩብ በአሜሪካ እና ሕንድ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማስታወቂያ በማይሄድባቸው አገራትም ለዩቲዩበሮች ገቢ ማግኛ አማራጭ ሆኗል። ግዙፉ የተንቀሳቃሽ ምስሎች ማጋሪያ አሁን 500 ሰብስክራይበር እና 3 ሺህ የዕይታ ሰዓት ካለዎ ገቢ ማግኘት ይቻላል ብሏል። ይህ ምን ማለት ነው? ከዩቲዩብ የሚገኘው ገቢ እንደ ኢትዮጵያ ወዳሉ አገራት እንዴት ይመጣል?


ቀድሞ የዩቲዩብ ገፅ ከፍተው ገቢ ለማግኘት ቢያንስ 1 ሺህ ደንበኛ [ሰብስክራይበር] መሰበሰብ ይጠበቅብዎ ነበር። አሁን ግን ዩቲዩብ ይህ ወደ 500 ዝቅ እንዲል አድርጊያለሁ ይላል።የዕይታ ሰዓቱም ወደ ሦስት ሺህ ዝቅ ብሏል። ለጊዜው ይህ የተፈቀደው በዩናይትድ ስቴትስ፣ በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)፣ በካናዳ፣ በታይዋን እና በደቡብ ኮሪያ ላሉ ተጠቃሚዎች ነው። ዩቲዩብ ትንሽ ከታገሳችሁኝ ይህን ሥርዓት በቅርቡ ለበርካታ አገራት አዳርሳለሁ ብሏል። ዩቲዩበሮች ከተንቀሳቃሽ ምስል ማጋሪያው የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ገንዘብ ማግኘት የሚችሉት ዩቲዩብ ፓርትነር ፕሮግራም በተሰኘው ማዕቀፍ ነው። ዩቲበኞች የዚህ ማዕቀፍ ተጠቃሚ ለመሆን 500 ሰብስክራይበር ሊያሰባስቡ እና በሦስት ወር ቢያንስ ሦስት ጊዜ ቪድዮ ሊጭኑ ይገባል። አሊያም 3 ሺህ ሰዓት ቪድዮዎቻቸው ሊታይ ይገባል። ካልሆነም 3 ሚሊዮን የዩቲዩብ ሾርት ዕይታ ማጋበስ አለባቸው።


ዋይዲ ቶም [YD TOM] በተሰኘ የዩቲዩብ ገፅ የሚታወቀው ይድዲያ ቶማስ 106 ሺህ ሰብስክራይበሮች አሉት። በዩቲዩብ እንዴት ገቢ ማግኘት ይቻላል? የሚለውን ጥያቄ ተንትኖ ይመልሳል። “ለምሳሌ አንድ የ10 ደቂቃ ቪድዮ ለጠፍክ እና 30 ሺህ ጊዜ ታየ እንበል” ይላል ይድዲያ። “ስለዚህ ይህንን የ10 ደቂቃ ቪድዮ በ30 ሺህ አስልቶ ወደ ሰዓት መቀየር ነው።ይህን ሥራ ዩቲዩብ ራሱ ነው የሚሠራው። ነገር ግን 10 ደቂቃ ሙሉ ሰው አያየው ይሆናል።” እንደሱ ገለፃ የ10 ደቂቃ ተለጠፈ ማለት ሰው ሙሉን ያየዋል ማለት አይደለም።አንዳንድ ሰው 5 ደቂቃ ተመልክቶ በቃኝ ሊል ይችላል። ነገር ግን ዩቲዩብ ‘አቬሬጅ ቪው ዱሬሽን’ የተሰኘ ቴክኖሎጂ አለው።ይህ በአማካይ ቪዲዮው ምን ያክል ታየ የሚለውን የሚተምን ነው።


ይድዲያ ዩቲዩበሮች ገቢ ለማግኘት ያለመታከት ብዙ ቪዲዮዎችን እንዲጭኑ ይመክራል። ነገር ግን በአንድ ቪዲዮም በርካታ ዕይታ ሊገኝ ይችላል።

“ለምሳሌ እኔ በአንድ ‘የፕራንክ’ ቪዲዮ ጭኜ ብዙ ሰው ያየልኝ። ሰላሳ፤ አርባ ሺህ ታየልኝ። አማካይ ዕይታው 4 ደቂቃ ነበር፤ ነገር ግን ሞላልኝ።”


ዩቲዩብ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ በይነ መረብ ብቅ ያለው በፈረንጆቹ ሚያዚያ 23/2005 ነበር።

የድርጅቱ ሽርክ መሥራች የሆነው ጃዌድ ካሪም ከዝሆኖች ፊት ቆሞ የለጠፈው የ19 ሰከንድ ተንቀሳቃሽ ምስል የመጀመሪያው የዩቲዩብ ይዘት ነው። ዩቲዩብ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ይዘት፤ራሳቸው ቀርፀው እንዲለጥፉ ያበረታታል። ለዚህ ነው ይድዲያ የቅጂ [ኮፒራይት] ጉዳይ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል የሚለው። የመጀመሪያው እርምጃ ግን ‘አፕላይ’ ማድረግ ነው። “ወደ ዩቲዩብ አካውንትህ ስትገባ የሞኒታይዜሽ (ገንዘብ የማግኛ) ቦታ አለ።አንድ ሺህ ሰብስክራይበር እና 4 ሺህ ሰዓት መታየቱን ለማመልክት አረንጓዴ ጭረት አለ። ሁለቱ አረንጓዴ ሲሆኑ ነው ‘አፕላይ’ የምታደርገው (የምታመለክተው) ።”

ተጠቃሚዎች የዩቲዩብ መስፈርት ካሟሉ በኋላ ገቢ ማግኛውን ተጭነው ይሁንታ እስኪሰጣቸው ከ24 አስከ 48 ሰዓታት ሊጠብቁ ይችላሉ። “ቪድዮ ጭነህ ገቢ ለማግኘት ‘አፕላይ’ ስታደርግ ዩቲዩብ ሊቀበልህም ላይቀበልህም ይችላል። ሜታዳታው ይታያል። ይዘቱ ከሰው የተወሰደ ነው ወይስ የግለሰቡ የራሱ ሥራ ነው ወይ? ቪድዮዎቹ ከየት ነው የመጡት? ራስህ የቀረፅከው ነው ወይ? የተጠቀምከው ሙዚቃ ከየት የመጣ ነው? ይሄ ሁሉ ይጣራል። ”ይዲድያ እንደሚለው የዕይታ ሰዓቱን መሥፈርት መሙላቱ ነው ዋናው ነገር፤ ሰብስክራይበር ማግኘት ብዙም ከባድ አይደለም።

እሱ ከልምዱ እንደሚያካፍለው ሰብስክራይበር በሰው በሰውም ቢሆን ሊሳካ ይችላል። ዋናው ቁምነገር የዕይታ ሰዓቱን ሰዎች በሚወዱት ይዘት ለማግኘት መጣር ነው።

የዩቲዩብ ብር ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ይመጣል? ይድዲያ “ኢትዮጵያ ውስጥ በዕይታም ሆነ በሰብስክራይበር ገቢ ማግኘት አይቻልም” ይላል። ምክንያቱ ደግሞ ማስታወቂያ በዩቲዩብ አለመሄዱ ነው። “አንድ ሚሊዮን ሰው ቢያይህ አንድ ብር አታገኝም። ነገር ግን ብዙ ሰው ባየልህ ቁጥር ቪዲዮው ‘ቫይራል’ ይሆናል [በስፋት ይሰራጫል] ። ይህንን ተከትሎ ሌሎች አገራት ያሉ ሰዎች ያዩታል።ይህም ገቢ ይሆናል።” ዘንድሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ዩቲዩብ እና ቲክቶክን ጨምሮ ዋና ዋና ማኅበራዊ ሚድያዎች ያለ ‘ቪፒኤን’ ማሰስ አይቻልም።

ይህ ለይዲድያ እና ለሥራ ጓደኞቹ የዕድሜ ባለፀጋ ‘ምርቃት’ ሆኗል።“ለምሳሌ እኛ ቪዲዮ ሲታይልን ከ50 አስከ 60 በመቶው ዕይታ ከኢትዮጵያ ነው።እኛ ገቢ የምናገኘው ከቀሪው 40 በመቶ ነው” ይላል። “አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ቪፒኤን’ ሲመጣ ገቢው መቶ በመቶ ሆነ። ገቢያችን በሦስት እና በአራት እጥፍ ጨመረ።” ዩቲዩበሮች ገቢ ለማግኘት መሥፈርት አሟልተው ‘አፕላይ’ የሚለውን ሲጫኑ ጉግል አድሴንስ ወደተባለው ገፅ በማምራት ሌላ ‘አካውንት’ እንዲፈጥሩ ይሆናል። ዩቲዩብ አድሴንስ ተጠቃሚዎች በበይነ መረብ ላይ ገቢ የሚያስገኝ ይዘት ሲለጥፉ ገንዘብ የሚያገኙበት ገፅ ነው። ይህ የአድሴንስ አካውንት ከዩቲዩብ ጋር ይገናኛል። “ገንዘብ ወደ ኪስህ የሚገባው 70 ዩሮ አሊያም 100 ዶላር እና ከዚያ በላይ ሲሆንልህ ነው።ወር ሲደርስ ይህ ብር ወደ አድሴንስ አካውንትህ ይሄዳል። አድሴንስ አካውንትህን ኢትዮጵያ ካለ የባንክ ሒሳብ ጋር ታያይዘዋለህ።” በቀላል አማርኛ ሲያስረዳ “ገንዘቡ ከዩቲዩብ አካውንትህ ወደ አድሴንስ ይሄዳል፤ ከዚያ ወደ ባንክ ሒሳብህ ይገባል” ይላል። እንደይዲድያ ገለፃ፤ ሌላኛው አማራጭ አንዳንድ ዩቲዩበሮች እንደሚያደርጉት ውጭ አገር ካለ የባንክ ሒሳብ ጋር አካውንቱን አገናኝቶ ገቢው በዶላር እንዲሆን ማድረግ ነው። ከአድሴንስ ጋር የባንክ ሒሳብ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የገንዘብ መላላኪያ መንገዶችን ማገናኘት ይቻላል። ይዲድያ ‘ሱፐር ቻት’ ስለተሰኘው የዩቲዩብ ገፅም ለቢቢሲ አማርኛ ይገልጻል። ሱፐር ቻት’ ማለት ልክ እንደ ቲክቶክ ሰብስክራይበሮች ስጦታ የሚሰጡበት ነው።ለምሳሌ አንድ ሰው ‘ታንክስ ካርድ’ ብሎ 100 ዶላር ስጦታ ሊሰጥህ ይችላል።

ዩቲዩብ ይዘት አዘጋጆችን ለማበረታታት ቀድሞ 1 ሺህ ሰብስክራይበር እና 4 ሺህ የዕይታ ሰዓት የነበረው አሁን ወደ 500 ተከታዮች እና 3 ሺህ የዕይታ ሰዓት ዝቅ ማለቱን ይናገራል።

ነገር ግን ይህ ለውጥ በአሁኑ ጊዜ በተወሰኑ አገራት ውስጥ ብቻ ተግባራዊ የሆነ ሲሆን፣ በቀጣይ ሌሎችንም አገራት እንደሚያካትት ተገልጿል።




4 views0 comments

Comentários


Post: Blog2 Post
bottom of page